ከሸዋ ሮቢት እስከ ሚሽጋን የተደረገ ትግልና የኢትዮጵያዊቷ ድል
ማክዳ በአይቲ ዘርፍ ባለሙያ ሲሆኑ ከአሜሪካ ታዋቂው ኤምአይቲ ዩኒቨርስቲ በሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ የተመረቁ ናቸው። ማክዳ የተወለዱት ሸዋ ሮቢት ሲሆን በዲቪ ሎተሪ እድል አሜሪካን ከ15 አመታት በፊት አቅንተዋል። በአሁኑ ወቅት በሚሽጋን ስቴት ከባለቤታቸው እና ከሁለት ልጆቻቸው ጋር ይኖራሉ። ማክዳ በአክሲዮን ገበያ ላይ ኢንቨስት ማድረግ የጀመሩት በ1,000 ዶላር ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት የተለያዩ ውጣ ውረዶችን አሳልፈዋል። ዛሬ ግን በጽናትና በእውቀት የታገዘ ኢንቨስትመንታቸው አስደናቂ ውጤት እያስገኘላቸው ይገኛል። ለአክብሮት ያህል ይህን ካልኩ ቃለ መጠይቁን አንቺ እያልኩ ቀጥያለሁ። መልካም ቆይታ!
By Dr Abush Ayalew
9/15/20241 min read


"ፈተናዎች ቢበዙም ተስፋ አትቁረጡ! በትጋትና በእውቀት የታገዘ ኢንቨስትመንት የፋይናንስ ነፃነትን ያስገኛል" ወ/ሮ ማክዳ አበበ
ዶ/ር አቡሽ፦ ማክዳ እንኳን ወደ አድዋ ትራንስፎርሜሽን ሴንተር ብሎግ በደህና መጣሽ! ስለ ኢንቨስትመንት ጉዞሽ እና ያገኘሽውን ስኬት ብታካፍይን ደስ ይለናል።
ማክዳ፦ እሺ ዶ/ር አቡሽ በደስታ! ተወልጀ ያደኩት በሸዋ ሮቢት ነው። በ17 ዓመቴ ነው አሜሪካ የመጣሁት። በትምህርቴ ሠቃይ ነበርኩ። ወደ አሜሪካ እንደመጣሁ ውጤቴ አግዞኝ የስኮላርሽፕ ዕድል አገኘሁና ኤም አይ ቲ በሶፍትዌር ኢንጅነሪንግ ተመረቅሁ። እዛ በነበርኩበት ጊዜ ነበር ስለ አክሲዮን ገበያ ኢንቨስትመንት መስማት የጀመርኩት። አንዳንድ ጓደኞቼ ቤተሰቦቻቸው የገዙላቸውን የስቶክ ትርፍ ሲያሳዪኝ ገበያውን መቀላቀል እንዳለብኝ ጉጉት አደረብኝ። መጀመሪያ ላይ በጣም ፈራሁኝ። ኢንቨስትመንት የባለጸጎች ጨዋታ እንደሆነ አድርጌ ነበር የማስበው። እኔ እንደ ተራ ሰው እዚያ ውስጥ ገብቼ ምን ላደርግ ነው የሚል ስሜት ነበረኝ።
ዶ/ር አቡሽ:- እውነት ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ ስቶክ ማርኬት ስላልነበረም የመስማት አጋጣሚው አይኖርሽም። በዚያ ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስተር ከተባለ ትልቅ ባለሐብት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። አሜሪካ ደግሞ በአንድ ዶላር ስቶክ የገዛውም ኢንቨስተር ነው የሚባለው (ፈገግታ)😃😃። ለመሆኑ አጀማመርሽ እንዴት ነበር?
ማክዳ :- ከአክሲዮን ጋር የመጀመሪያዬ ግንኙነቴ - ልክ እንደ ህጻን ልጅ የሚያምር ነገር ሲያይ እንደሚደነቅ ሁሉ እኔም በአክሲዮን ገበያ ውበት ተማርኬ ነበር። ነገር ግን ይህ ውበት በፍጥነት ወደ ድንጋጤ ተቀየረ። የገዛሁት የመጀመሪያው አክሲዮን ዋጋ በአንድ ቀን ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ሲወርድ ራሴን ነበር የያዝኩት። ያኔ እንደ ጀማሪ የገበያውን ተለዋዋጭነት በአንዴ ተረዳሁ። በእውነቱ ለመናገር ልቤ እንደከበሮ ድው ድው ሲል ይሠማኝ ነበር (ሳቅ)::
ያኔ እንደ ጀማሪ ባለሀብት አክሲዮን መግዛት ልክ እንደ ሽሮ ወጥ መብላት መስሎኝ ነበር - ጣፋጭ ነበር ግን መጨረሻው ቁርጥማት ነበር የሆነብኝ (ሳቅ)😀
ዶ/ር አቡሽ፦ ታዲያ ፍርሃትሽን እንዴት አሳልፈሽ ልትቀጥይበት ቻልሽ?
ማክዳ፦ እንደ ኢትዮጵያዊ ሴት በደሜ ውስጥ የአድዋ መንፈስ አለ። አባቶቻችን አድዋ*ላይ ድል ያደረጉት በጀግንነት፣ በአንድነት እና በብልሃት ነው። እኔም እነዚህን እሴቶች በኢንቨስትመንት ዓለም ውስጥ ተግባራዊ አደርጋቸው ነበር። መጀመሪያ ላይ በጣም በጥንቃቄ ነበር የተራመድኩት። አንድ ሺህ ዶላር ብቻ ነበረኝ፤ ያንንም ላጣው አልፈለኩም ነበር።
ዶ/ር አቡሽ፦ እንደ ጀማሪ ባለሀብት ምን አይነት ችግሮች እንደገጠሙሽ አጫውችን?
ማክዳ፦ ኧረ ብዙ ነበሩ! መጀመሪያ ላይ ገበያው እንደ ውቅያኖስ ነበር የሚታየኝ፤ ሰምቼው የማላውቀው ቃላት ያዘንቡብኛል።
"የአክሲዮን ገበያ ቋንቋ" - እንግሊዝኛ አዲስ እንደሆነብኝ ሁሉ የአክሲዮን ገበያ ቃላቶችም እንግዳ ነበሩ። አንድ ቀን አንድ የፋይናንስ ዜና ሳነብ እራሴን ልክ ባዕድ አገር ውስጥ እንደጠፋ ሰው ሆኖ ተሰማኝ። በቃላት ባህር ውስጥ እየዋኘሁ ነበር! ይታይህ እንግሊዝኛ የሚችለኝ የለም፤ በስቶክ ማርኬት እንግሊዝኛ ግን ጦጣ ነበር የሆንኩት። እኔ ደግሞ አልጀምር እንጅ ከጀመርኩ እልኸኛ ነኝ። ስለዚህ ተስፋ ሳያስቆርጠኝ ነበር የቀጠልኩት።
ዶ/ር አቡሽ፦ እውነት ነው ብዙ እንግዳ ቃላቶች አሉት። እነዚህን ፈተናዎች እንዴት አሸነፍሻቸው ታዲያ? ምን ዓይነት ስልቶችን ተጠቀምሽ?
ማክዳ፦ ትምህርት ቁልፍ ነው። ያለማቋረጥ ስለ ኢንቨስትመንት፣ ስለ አክሲዮን ገበያ እና ስለ ኢኮኖሚ አንብቤያለሁ። ከባለሙያዎች ምክር ወስጃለሁ። እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ተግባራዊ ልምምድ አድርጌያለሁ። በትንሽ ገንዘብ ጀምሬ እየተማርኩ እያደግኩ መጣሁ።
ዶ/ር አቡሽ፦ በአክሲዮን ገበያ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ጀማሪዎች ምን ምክር አለሽ?
ማክዳ፦ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ኢንቨስትመንት የረጅም ጊዜ ጉዞ መሆኑን ይረዱ። በአንድ ጀምበር ባለጠጋ ለመሆን አይቻልም። ሁለተኛ፣ ትምህርት ወሳኝ ነው። ስለ ገበያው፣ ስለ ኢኮኖሚው እና ስለሚፈልጉት የኢንቨስትመንት አይነት በደንብ ይረዱ። ባለሙያዎችን ያማክሩ። እና ከሁሉም በላይ ደግሞ አይፍሩ።
ዶ/ር አቡሽ፦ አንቺ እንደ አንዲት ሴት እና ከስደተኛ ቤተሰብ የመጣሽ ሰው በኢንቨስትመንት ዓለም ውስጥ ምን አይነት ልዩ ተግዳሮቶች አጋጥመውሻል?
ማክዳ፦ እውነቱን ለመናገር መጀመሪያ ላይ የኢንቨስትመንት ዓለም ለእኔ እንግዳ ነበር። ብዙ ጊዜ እኔ እዚህ የምገባበት ቦታ የለኝም የሚል ስሜት ይሰማኝ ነበር። በተለይ በቴክኖሎጂ ዘርፍ እንደ ሴት አንዳንድ ጊዜ ተቀባይነት ለማግኘት እታገል ነበር። ሶፍትዌር ኢንጂነር ነኝ፤ ይህ እውቀቴ ግን በስቶክ ማርኬት ውስጥ ቦታ አልነበረውም።
በተለይ እንደ ሴት ኢንቨስተር የሚደርስብኝ አመለካከት ደግሞ በጣም ይገርምሀል - አንድ ቀን በምኖርበት ካውንቲ አንድ የኢንቨስትመንት ሴሚናር ላይ ስገኝ አንድ ሰው ወደ እኔ መጥቶ "ይቅርታ ቡና ታመጭልኝ?" ሲለኝ በጣም ተናደድኩ። እባክህ አንተ ታመጣልኝ ልለው አሠብኩና ከአፌ ላይ መለስኩት። እኔ እዚያ የነበርኩት እንደ ተሳታፊ እንጂ እንደ አስተናጋጅ አልነበረም። ያኔ እንደ ሴት በዚህ መስክ ገና ብዙ መሰናክሎች እንዳሉ ተገነዘብኩ። ያው በዚያ ላይ ጥቁር ስትሆን ደግሞ አመለካከታቸው ቀላል አይደለም።
ዶ/ር አቡሽ፦ እነዚህን ተግዳሮቶች እንዴት ተወጣሽዋቸው?
ማክዳ፦ በራሴ እምነት ነበረኝ። እኔም እንደማንኛውም ሰው ስኬታማ መሆን እንደምችል አውቅ ነበር። እውቀቴን አበልጽጌያለሁ፣ ከሌሎች ሴት ባለሀብቶች ጋር ተባብሬያለሁ፣ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ ተስፋ አልቆረጥኩም።
ዶ/ር አቡሽ፦ በኢንቨስትመንት ጉዞሽ ያጋጠሙሽ አስቂኝ ወይም የማይረሱ ትዝታዎች አሉ? ብታካፍሊን?
ማክዳ፦ አንድ ጊዜ አንድ "hot tip" ሰምቼ ያለ ምንም ጥናት በአንድ ኩባንያ ላይ ኢንቨስት አደረግሁ። በሚቀጥለው ቀን አክሲዮኑ ወደቀ! ያን ጊዜ ትምህርቴን በደንብ ተምሬያለሁ - ሁሌም መመርመር እና የራሴን ጥናት ማድረግ ነበረብኝ። በእርግጠኝነት እበላለሁ ብየ ነበር ግን ተበላሁ። ሳቅ😀😀
ዶ/ር አቡሽ፦ ከሶስት ዓመት በፊት ወደኢትዮጵያ ስትመጭ በእኛ ሠሚናር ላይ በተሳተፍሽ ጊዜ ነበር የተዋወቅነው። የሠሚናሩ ትምህርት በኢንቨስትመንት ስትራቴጂሽ ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?
ማክዳ፦ እጅግ በጣም ብዙ! ስልጠናው የገበያውን መሰረታዊ ነገሮች በሚገባ እንድረዳ አድርጎኛል። ስሜቴን ተከትዬ ውሳኔ አለማድረግን ተምሬያለሁ። እናም ከሁሉም በላይ ደግሞ ታጋሽ መሆንን ተምሬያለሁ። የተለያዩ ኢንቨስትመንቶችን በማድረግ የኪሳራ ዕድልን መቀነስ ምን ያህል ወሳኝ እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ለምሳሌ ያህል እኔ እንደ ኡበር፣ ኤክሶን ሞቢል፣ ኤንቪዲያ እና አማዞን ባሉ ኩባንያዎች ላይ ኢንቨስት አድርጌያለሁ። እንዲሁም የመንግስት ቦንድ እና እንደ ቫንጋርድ ባሉ ኢንዴክስ ፈንዶች ላይም ኢንቨስትመንት አለኝ። ይህ የተለያየ አይነት ኢንቨስትመንት የኪሳራ አደጋየን ለመቀነስ አግዞኛል። ሠሚናሩ በነበረኝ እውቀት ላይ ይበልጥ ጨምሮልኛል።
ዶ/ር አቡሽ፦ እናመሠግናለን ማክዳ። ኢንቨስት ያደረግሽባቸው በጣም ጥሩ ምርጫዎች ይመስላሉ። በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። በዚህ ወቅት ኢንቨስት ለማድረግ ለሚፈልጉ ሰዎች ምን ምክር አለሽ? አንችስ እንዴት እያለፍሽበት ነው?
ማክዳ፦ አዎ፣ በአሁኑ ወቅት ኢኮኖሚው አስቸጋሪ ነው። በአንድ በኩል ጥሩ ነገር አለ፤ ኢንፍሌሽን እየቀነሠ ነው፤ ወለድ መቀነስ ጀምሯል። የኢኮኖሚው ሁኔታ ግን ገና አለየለትም። በዚያ ላይ በምርጫ ላይ ነን። በእርግጠኝነት ትራምፕ ካሸነፈ ገበያው በጣም ስለሚዋዠቅ ከወዲሁ ሠግተናል። ነገር ግን ይህ ማለት ኢንቨስት ማድረግ የለብንም ማለት አይደለም። ወሳኙ ነገር በጥንቃቄ መምረጥ እና በረጅም ጊዜ እድገት ላይ ማተኮር ነው። እንደ ክሪፕቶከረንሲ እና ዴይ ትሬዲንግ ያሉ ከፍተኛ ተለዋዋጭነት ያላቸውን ኢንቨስትመንቶች እኔ ብዙም አልወዳቸውም። ይልቁንስ በተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ በማተኮር አደጋን መቀነስ እመርጣለሁ።
ዶ/ር አቡሽ፦ የአድዋ ድል በኢንቨስትመንት ጉዞሽ ላይ ምን ተጽእኖ ይኖረዋል ብለሽ ታስቢያለሽ?
ማክዳ፦ የአድዋ ድል ለእኔ የማይበገር መንፈስ ምንጭ ነው። ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን በአድዋ የጣሊያንን ጦር ድል ማድረግ ከቻሉ እኔም በገበያ ውስጥ ያሉ ተግዳሮቶችን አልፌ ማሸነፍ እችላለሁ የሚል እምነት ይሠጠኛል። ዛሬ አድዋ ያለው ሠሜን ኢትዮጵያ አይደለም። የእያንዳንዳችን ህይዎት በራሡ አድዋ ነው። ህይዎት ትግል ነው። እኛ ደግሞ አዝማችም ዘማችም ነን። በተለይ ደግሞ ከድፍረት ባሻገር በኢንቨስትመንት ውስጥ ትዕግስት እና ጽናት ወሳኝ መሆኑንም የአድዋ ዘመቻ ያስተምረናል ብየ አስባለሁ።
ዶ/ር አቡሽ፦ ለወደፊቱ በኢንቨስትመንት ስትራቴጂሽ ላይ ምን ለውጦችን ለማድረግ አስበሻል?
ማክዳ፦ እውቀቴን ማሳደግ እና አዳዲስ የኢንቨስትመንት አማራጮችን መፈተሽ እቀጥላለሁ። በተለይ በአርቴፊሻል ኢንተሊጀንስና በታዳሽ ሀይል ስቶኮች ላይ በደነብ ማተኮር እንዳለብኝ አስባለሁ። የኤንቪዲያ ስቶክ ብቻ በቂ አይደለም። በተጨማሪም ልምዴን ለሌሎች በማካፈል እና በተለይ ለሴቶች የኢንቨስትመንትን አስፈላጊነት በማስተማር ላይ አተኩራለሁ። እንዲሁም ልጆቼን ገና ከጅምሩ ስለ ገንዘብ እና ኢንቨስትመንት ማስተማር ጀምሬያለሁ።
አንዳንዴ አበሾች ስለ ኢንቨስትመንቶቼ ሲጠይቁኝ እኔም "እሺ በቃ ገንዘቤን ወስጄ በትራስ ውስጥ እደብቀዋለሁ ፤ ከዚያ ወልዶ ያድራል" እላቸዋለሁ። ግራ ሲጋቡ ፈገግ እልና "እውነቱን ልንገራችሁ ኢንቨስት ማድረግ ልክ እንደ ጥሩ ቡና መቅመስ ነው። መጀመሪያ ላይ ትንሽ መራራ ሊሆን ይችላል መጨረሻው ግን አስደሳች ነው" እላቸዋለሁ። አንዳንዶቹ ደግሞ ቀልደኞች ናቸው (ፈገግታ) እስኪ በጣም የሚመች ስቶክ ንገሪኝ የሚሉኝም አሉ።
ዶ/ር አቡሽ:- ምን እንዲገዙ ትጠቁሚያቸዋለሽ?
ማክዳ:- 😃😃 ሳቅ። የሚመች ነገር መግዛት ከፈለጉማ አሪፍ ስፖንጅ ፍራሽ ገዝተው ይተኙ። (ሳቅ) ስቶክ ማርኬት ውስጥ እንደዛ ብሎ ነገር የለም። ስቶክ ማርኬት በአስቀያሚም በአስደሳችም ትዕይንቶች የተሞላ ነው። ደረቅ ወለል ላይ እንደመተኛት ነው። እየቆረቆረህ የምትተኛበት።
ዶ/ር አቡሽ፦ በጣም ጥሩ አገላለፅ ነው። በነገራችን ላይ ልጆችን በለጋ እድሜ ስለ ፋይናንስ ማስተማር በጣም አስፈላጊ ነው።እኔም ልጆቼን አስተምሪያለሁ። ባለቤትሽ ግን ስለ ኢንቨስትመንት ጉዞሽ ምን ይልሻል? ያበረታሻል?
ማክዳ፦ (ፈገግታ) መጀመሪያ ላይ እንዳቆም ይመክረኝ ነበር። አደጋው እንደሚያስጨንቀው ይነግረኝ ነበር። ነገር ግን በትጋት ስሰራ እና ውጤቶችን ማስገኘት ስጀምር አመለካከቱ ተቀየረ። አሁን እሱ ራሱ ከአኔ ብሷል (ሳቅ)።
ዶ/ር አቡሽ፦ ለኢትዮጵያውያን ሴቶች በተለይ በኢንቨስትመንት ዙሪያ ምን ማለት ትፈልጊያለሽ?
ማክዳ፦ ምንም እንኳን ፈታኝ ቢሆንም በኢንቨስትመንት ዓለም ውስጥ እራሳችሁን አታግልሉ። ተማሩ፤ አደጋዎችን ተረዱ፣ እና በራሳችሁ አቅም እምነት ይኑራችሁ። እኔ ከቻልኩ እናንተም በእጥፍ ትችላላችሁ ማለት እወዳለሁ። በተለይ የሴቶች ባህሪ ለኢንቨስትመንት ጥሩ ነው፤ እንደወንዶች አይደለንም። ትዕግስቱ አለን። ይሁን እንጅ ወንዶች ደግሞ ሪስክ በመውሰድ ድፍረታቸው ይበልጡናል። ስለዚህ አንፍራ ነው የምላቸው።
ውድ አንባቢዎች፣
የማክዳ ታሪክ የሚያሳየን በትጋት፣ በዕውቀት እና በድፍረት የታገዘ ማንኛውም ሰው የፋይናንስ ነፃነቱን ማግኘት እንደሚችል ነው። በአድዋ ትራንስፎርሜሽን ማዕከል የምናቀርበው አለም አቀፍ የስቶክ ገበያ ስልጠና እርስዎም ይህንን ስኬት እንዲያገኙ ይረዳዎታል።
በስልጠናው ወቅት የሚያገኙት
ስለ ኢትዮጵያ እና አለምአቀፍ የአክሲዮን ገበያዎች ጥልቅ ግንዛቤ
ከተሞክሮ ባለሙያዎች የሚሰጥ ቀጥተኛ እገዛ እና ክትትል
በተጨባጭ የገበያ ሁኔታዎች ላይ የሚያሠለጥኑ ልምምዶች
የኢንቨስትመንት ስትራቴጂዎችን በተግባር የመተርጎም ችሎታ
ከሌሎች ተማሪዎች ጋር የመረዳዳት እና የመተጋገዝ ዕድል
For more information, visit our website
ዛሬውኑ ይመዝገቡ እና የፋይናንስ ነፃነት ጉዞዎን ይጀምሩ!
አድዋ ትራንስፎርሜሽን ሴንተር - የፋይናንስ ህልምዎትን እውን ለማድረግ ከጎንዎ ነን!
ይህን አነቃቂ ጽሑፍ ለወዳጅ ዘመድዎ ሼር በማድረግ የእነሱንም የፋይናንስ ነፃነት ጉዞ እንዲጀምሩ ያግዟቸው።